image
image
image
image
image

"የሸማች ማህበራት ሪፎርም እና ገበያ ማረጋጋት ስራችን የለውጡ አንድ አካል ናቸው።" ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ

ሚያዚያ 1, 2018
በልደታ ክፍለ ከተማ አዲስ ሚሊኒየም ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር የገበያ ማዕከል በዛሬው እለት በድምቀት ተመርቆ ለግብይት ክፍት ሆነ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ክቡር አቶ ጃንጥራር አባይ በገበያ ማዕከሉ ምረቃ ፕሮግራም ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉ ሲሆን የሸማች ማህበራት ሪፎርም እና ገበያ ማረጋጋት ስራችን የለውጡ አንድ አካል ናቸው ብለዋል። ሸማች ማህበራቱ የምርት አቅርቦች ችግር በሚኖርበት ጊዜ መልስ ሰጪ ናቸው ያሉት ክቡር ምክትል ከንቲባው በበዓላት ወቅት የሚከሰተውን ሰው ሰራሽ የምርት እጥረት እና የዋጋ ንረት ለመከላከል ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልፀዋል። ክቡር አቶ ጃንጥራር አያይዘው በአሁኑ ወቅት በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተው አጠቃላይ አለማቀፋዊ ቀውስን ታሳቢ ያደረገ የዋጋ ማረጋጋትና የምርት አቅርቦት ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከአምራች አርሶ አደሮች በቀጥታ ለሸማቹ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው እንደነዚህ አይነት የገበያ ማዕከላት ተደራሽ ማድረግ ህብረተሰቡ በህገወጥ ደላሎች እና በትራንስፖርት ችግር ይደርስበት የነበረውን እንግልት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንሰው አስገንዝበዋል። ወ/ሮ ሊዲያ አያይዘው የበዓላት ወቅት በመጠቀም ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ፣ በምርቶች ላይ ባዕድ ነገሮችን የሚቀላቅሉ፣ በመጋዘን በህገወጥ መንገድ የሚከዝኑ እንዲሁም ከሀሰተኛ የብር ኖት ግብይት ጋር በተያያዘ ማህበረሰቡ ራሱን እንዲጠብቅና ለሚመለከተው የህግ አካል ጥቆማ እንዲያደርግ አሳስበዋል። የክ/ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ልዕልቲ ግደይ እንዳሉት የፋሲካ በዓል ባዛር ምክንያት በማድረግ በዛሬው እለት የተከፈተው ማዕከል ከዚህ ቀደም ለግለሰቦች በኪራይ መልክ በማስተላለፍ ለጥቂቶች መጠቀሚያ የነበረ ሲሆን ሆኖም አስተዳደሩ በጀመረው ሪፎርም መሠረት አሁን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን የሚያቀርብ የገበያ ማዕከል ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል። የኑሮው ውድነት የማረጋጋት ስራ ከሌሎች ፕሮጀክቶች ባልተናነሰ የቅድሚያ ቅድሚያ እየተሰጠው መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ ልዕልቲ የከተማው አስተዳደር የኑሮ ውድነትና ገበያ ማረጋጋት ግብረ ሀይል ትላልቅ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል። በተያያዘ 'በቂ አቅርቦት ከአምራች እስከ ሸማች በተመጣጣኝ ዋጋ ለፋሲካችን' በሚል መሪ ቃል የመጪው የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በክፍለ ከተማው የተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ የበዓል ባዛር እና ኤግዝቢሽን ማዕከላት በተመጣጣኝ ዋጋ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶች እየቀረበ ይገኛል።

መልዕክትዎን ይላኩ